ማውጫ 2

ደራሲ: editorial staff

ውድ አንባቢያን፣

 

የእግዚአብሔር ቃል «አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።» (ማቴ. 6፡33) ይላል።

ይህ ቃል እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ ልንሰጠው እንደሚገባና ሌሎች ጉዳዮች ሁሉ (ለምሳሌ የግል እቅዶቻችን፣ ምኞቶቻችን፣ ፍላጎቶቻችን፣ በምንኖርባት ዓለም አምረውና ደምቀው የሚታዩ ነገሮች በሙሉ በሕይወታችን የሚያስፈሩ መስለው የሚታዩ ችግሮች ሸክሞች በሽታዎች ወዘተ) በሙሉ ሁለተኛ ደረጃ ሆነው ሊወሰዱ የሚገባቸው መሆኑን የሚመክር ነው። ለዚህም ነው ጳውሎስ «እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?» (ሮሜ. 8፡31) በማለት የእግዚአብሔርን ቀዳሚነት አጉልቶ ያወጣው። ጳውሎስም ይህንን ያለው በምእራፍ 7 ወደሞት ከሚወስደኝ ከዚህ ሰውነት ማን ሊለየኝ ይችላል በማለት የልብ ጩኸት (ለቅሶ) ካሰማ በኋላ እንደ መልስ ከመንፈስ ቅዱስ የተቀበለው መልእክት ነው። ይህም በምእራፍ 8፡1 ላይ «በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም» በማለት በምእራፍ 7 ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል።

በዘመናችን ያለነው በክርስቶስ ደም ተዋጅቶ በቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ምሥጢራዊ አካል ተገጣጥመን የምንገኘውና ሌሎችም በታላቅ ፈተና ውስጥ እንደሚገኙ ለማንም የተሰወረ አይደለም። ይሁዳ በመልእክቱ በቁጥር 23 «አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ» እንዳለው ይህች በእግዚአብሔር ታላላቅ ሥራዎች የተሞላች መጽሔት እንደ ጳውሎስ እርዳታን ፈልጋ ለምትጮህ ነፍስ ምላሽ ናት ብዬ አምናለሁኝ።

ስለዚህ አንባብያን በእዚህ መጽሔት ውስጥ በምታገኙት ምስክርነት በእግዚአብሔር ጸጋ እንደምትባረኩ አምናለሁና፤ ተያይዞ ግን ሌሎች ይህንን አገልግሎት እንደሚያገኙ መጽሔቱን በማድረስ ወይንም ሌሎች ይህንን መልካም ዜና እንዲሰሙ በማድረግ የበኩላችሁን ተልእኮ እንድትወጡ አደራ እላለሁኝ።

 

+ አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

ያለፈው   |   የምሚቀጥለው በስተጀርባ

Copyright © Wydawnictwo Agape Sp. z o.o. ul. Panny Marii 4, 60-962 Poznań, tel./ fax: 61/ 852 32 82 | tel. 61/ 647 26 86